አዲስ አበባ የካቲት 1/2002(ሬዲዮ ፋና) ዛሬ በብሄራዊ የምርጫ ቦርድ መሰብሰቢያ አዳራሽ የየፓርቲዎቹ ተወካዎች የመገናኛ ብዙሀን አጠቃቀምን በሚመለከት ውይይት ለማድረግና የእጣ አወጣጥ ስነ-ስርአት ለማካሄድ የተሰባሰቡ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ ከአባላቶቻቸው ጋር ለመወያየት በማሰብ ፕሮግራሙን ለረቡዕ አስተላልፈውታል።
ይሁንና የሰአት ድልድል በሚመለከት የተዘጋጀውን ፅሁፍ በደንብ እንየው ብሎም ከአባሎቻችን ጋር እንወያይበት በሚል ምክንያት ፕሮግራሙን ከነገ በስቲያ ጧት ለማካሄድ ከስምምት ደርሰዋል።
በዛሬው መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ብሮድ ካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ደስታ ተስፋው እንዳሉት የሰአት ድልድሉ የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድና የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ የተዘጋጀ ነው።
አሁን የተዘጋጀው የመገናኛ ብዙሀን የሰአት ድልድል ፓርቲዎች ፕሮግራሞቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ብቻ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደስታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርን በሚመለከት ግን ፓርቲዎቹና የመገናኛ ብዙሀኑ በጋራ ሊወያዩበት የሚችሉ መሆኑን አስምረውበታል።
በሰአት ድልድሉ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከመጪው ሀሙስ ጀምሮ ፕሮግራሞቻቸውን ማስተዋወቅ ይጀምራሉ።