አዲስአበባ፣ሐምሌ24 2002 (ሬዲዮፋና)በኢትዮጵያ መንግሥትና በተባበረው የምዕራብ ሶማሌ ነጻ አውጪ ግንባር መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት የሕዝቦች የጋራ ጥቅም ያገናዘበ መሆኑንየኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ገለጹ፡፡
የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አብዱላሂ አህመድ ኢብራሂም ለኢዜአ እንደተናገሩት በሁለቱ ወገኖች የተደረሰው ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡
ይህም በክልሉ ብሎም በአገሪቱ የተጀመረው የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች አጠናክሮ ለመቀጠል መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ሕዝብ በአገሪቱ ከተጀመረው ልማትና ዴሞክራሲ ተጠቃሚ መሆን መቻሉ እንደ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ያሉ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ጫና እያሳደረባቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ድርጅታቸው ሕዝቡ ባሳደረበትን ጫና ተከታታይ ውይይትና ግምገማ በማድረግ እንደ ቀሪው የአገሪቱ ሕዝብ የልማትና የዕድገት ጎዳናውን በመምረጥ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ መወሰኑን አቶ አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከግንባሩ ሦስት አራተኛው የሚበልጡ የአመራር አባላት በሕገ-መንግሥቱ ጥላ ሥር ሆነው ዓላማቸውን ለማስፈጸም መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሲሶ የማይሞላው ከኦብነግ ያፈነገጠው አንጃ የሕዝብ ድጋፍ እንደሌለው አቶ አብዱላሂ አስታውቀዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መንግሥትጋር እየተደረገ ያለው ስምምነት ልክ የተባበረውየምዕራብ ሶማሌ ነጻ አውጪግንባርእንዳደረገው ሁሉ፤ስኬታማ እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከግንባሩ ጋር የተደረሰው ስምምነት ሕዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ ልማትን ለማፋጠን የሚያስችል በመሆኑ አብነግም ለሰላም መቆሙን ማረጋገጥ ይገባዋል ብለዋል፡፡
አቶ አብዱላሂ አህመድ ኢብራሂም የግንባሩ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከመሆናቸው ሌላ፤ በአሥመራ የኦብነግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ለአምስት ዓመታት ማገልገላቸውን መናገራቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡