አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22 2002 (ሬዲዮ ፋና) ኢትዮጵያ ባለሃብቶች በሻይ ቅጠል ልማት ለመሰማራት የሚችሉበት ከስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬትና አመቺ ሁኔታ እንዳላት የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር አመለከተ፡፡
ለልማቱ የሚሆነው መሬት በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላና በአማራ ክልሎች በስፋት እንደሚገኝ የገለጸው ሚኒስቴሩ የአገሪቱ የደጋ ሻይ ጣዕም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነትና ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን አመልክቷል፡፡
በአገራችን በአሁኑ ጊዜ በሻይ ቅጠል የለማው መሬት 2 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑንና ከዚህም የሚገኘው ዓመታዊ ምርት ከሰባት ሺህ ቶን እንደማይበልጥ ተገልጿል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ይህንን መሠረት በማድረግም ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው የሻይ ቅጠል ልማት ቢዝነስ ዕቅድ ባለሃብቶች ሰባት ሺህ ሄክታር በሚደርስ መሬት ላይ ልማቱን እያካሄዱ ናቸው።